ሕፃናት እውነት ተናጋሪ ናቸው ። የሚወዱትን በግልጽ ይወዳሉ ፣ የማይፈልጉትንም ይሸሻሉ ። ቃላትን ለማሳመር አይጥሩም ፣ አሳባቸውን ለመግለጥ ይሞክራሉ እንጂ በቋንቋቸው ደካማነት አይሸማቀቁም ። እውነት የሚናገር ሰው በበዛ ቍጥር የድሆች መከራ ፣ የምስኪኖች መገፋት ይቆማል ። ይህ አንደበታችን አንድ ቀን ይታሰራል ፣ እውነትን መናገር ይገባዋል ። እውነታችን ደረቅ ከሆነ ይሰብራል ፣ ርጥብ ከሆነ ይዝለፈለፋል ። እውነታችን ፍቅር ያለው ሊሆን ይገባዋል ። እውነት የመናገራችን ዓላማ ሰውዬው እንዲለወጥ ብቻ ነው ። ያንን ሰው ለንስሐ ስንጋብዘው አብረን ንስሐ በመግባት ሊሆን ይገባዋል ። ዋጋ የለኝም ብሎ ራሱን እንዲጥል ሳይሆን ዋጋ አለኝ ብሎ እንዲነሣሣ ንስሐን መስበክ ይገባል ። ምግብ ሠርተን እንዲበላልን የምንፈልገው ሰው ካለ አብረነው እንበላለን ። ንስሐ አብረን የምንካፈለው መንፈሳዊ ገበታ ነው ። ስብከታችን ንስሐ ግቡ የሚል ቢሆንም ልባችን ግን ንስሐ እንግባ የሚል መሆን አለበት ። የንስሐ ስብከት ሰዎችን ማሸማቀቂያ ሳይሆን ለምድር ሰላም የምንመኝበት ነው ። ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ካልታረቀ ከራሱና ከሰዎች ጋር በሰላም መኖር አይችልምና ። የንስሐ ስብከት የፍቅር ስብከት እንጂ የእልህ ንግግር አይደለም ። አባትና ልጅ እንዲታረቁ መናፈቅ እንጂ የእግዚአብሔር ፖሊስ ሁኖ ማጋለጥ አይደለም ። ሕፃናት እውነት ሲናገሩ በገርነት ነው ። እንደውም ለሰዎች ንስሐንና ተግሣጽን ከተናገርን በኋላ ወደ ቤታችን ገብተን ስለ ራሳችን ኃጢአት ማልቀስ ፣ ለሰዎቹም መማለድ ይገባናል ።
ሕፃናት የውሸት ግንኙነት የላቸውም ። የሚወደዱትም ለዚህ ነው ። ሁሉን ወዳጅ ለማድረግ የሚፈልግ ሰው በመጨረሻ ላይ ምንም ወዳጅ አይኖረውም ። ሁሉም ወዳጅ ፣ ሁሉም ጠላት ሊሆን አይችልም ። ሁሉን ልንወድ እንችላለን ፣ ሁሉን ግን ወደ ሕይወታችን ማምጣት አይገባም ። ለሁሉም የቅን አመለካከት መያዝ መልካም ነው ፣ ከሰዎች ጋር ላለን ግንኙነት ጥንቃቄ እጅግ ወሳኝ ነው ። ሰዎች የቤተሰባቸው ፣ የአስተዳደጋቸው ፣ የውጣ ውረዳቸው ፣ የአመለካከታቸው ፣ የትምህርታቸውና የእምነታቸው ውጤት ናቸውና እንደ እኔ ካልሆኑ ብለን ማሰብ አይገባንም ። አቋማችን ግልጽ ሲሆን ሁሉም ያከብርልናል ። ተለዋዋጭነት ካለን ግን ሁሉም ይንቀናል ። ብዙ ውሸታሞችና አድር ባዮች በጊዜ ሲሞቱ ሐቀኞች ግን ዕድሜአቸው ይረዝማል ። የሁልጊዜ ተቺ መሆንም ያስንቃልና የተግባር ሰው ሁኖ ማስተማርን መልመድ አለብን ። እውነትን እንድንናገር ብቻ ሳይሆን እንድንኖረውም ወደ ምድር መጥተናል ። “ብዙ ቢያወጉ ይዘነጉ ፣ ብዙ ቢተቹ ይሰለቹ” ይባላል ። መድረኮች ስለ ተገኙ ሁሉ ጋ ተናጋሪ መሆን አይገባም ፣ ያየነውን ሁሉ የትችት ርአስ ማድረግም አስፈላጊ አይደለም ። ለሥራ ተፈጠርን እንጂ ሌሎችን ለመጎንተል አልተፈጠርንም ። ቋሚ ጠባይ ሲኖረን ሰዎች የሚቀርቡን አምነውበት ነው ።
እውነትን መኖር ያስፈልጋል ። ሰው በአቅሙ መብላት ፣ መጠጣት አለበት ። ከቻለ ሀብታም ቢሆን መልካም ነው ፣ ሀብታም ለመምሰል መሞከር ግን አስፈላጊ አይደለም ። ብዙ የኢትዮጵያ ወጣት ተታሎአል ። በሁለት ጆሮው የጆሮ ማዳመጫ ሰክቶ መሄድ ፣ በደማቅ አካባቢዎች ላይ ተበድሮ ሻይ መጠጣት የሕይወቱ ግብ አድርጎታል ። የሌላቸውን አለኝ በማለት የተለከፉ ፣ ውሸታቸውን እየረሱት ትዝብት ላይ የሚወድቁ ብዙዎች ናቸው ። መሆን እያለ መምሰል አስፈላጊ አይደለም ። ጎበዝ ቋንቋ አዋቂ መሆን ጥሩ ነው ። ግን ብዙ ቋንቋ የሚያውቁ አብዛኛውን ጊዜ ውሸትን ፣ አምታቶ መኖርን ሥራቸው ያደርጉታል ። ዓለም ጠባብ ነውና ብዘ ነገሮች እየተዘጉ እንደሚመጡ ይረሳሉ ። ስንናገር ስለ ቋንቋ ጥራት ሳይሆን ስለ አሳቡ እውነትነት መጨነቅ አለብን ። ቋንቋ እንዳይሰበርበት የሚጠነቀቀው ወገናችን ሰባራ አስተሳሰብ ግን ይዞ ሲጓዝ አይጨነቅም ።
ሕፃናት የሚደሰቱት በትንሽ ነገር ነው ። የሚያስፈልጋቸውን ብቻ ይጠይቃሉ ። የሚያስፈልገው ጥቂት ነው ። ሰው ሁሉ ለዛሬው መሻቱ ብቻ ቢያስብ ደስተኛ ይሆን ነበር ። ሰዎች የለበሱትን ለመልበስ ፣ ሰዎች የያዙትን ንብረት ለመያዝ መሮጥ ሕይወትን ፉክክር ውስጥ ይከታል ። በደረጃ ከማደግ ከፍ ያለ ማማ ላይ በአንድ ጊዜ ስለ መውጣት ማሰብ አይገባም ። ደስታን በጣም እያራቅናት ነው ። የሚያስፈልገንን ነገር መለየትና በዚያ ማመስገን ደስታ ያመጣል ። ሕፃናት የአእምሮ ሥዕል በመሳልና ያንንም በመሞከር የታወቁ ናቸው ። በሽቦ መኪና ይሠራሉ ፣ በደስታ ያሽከረክራሉ ። በወረቀት የአውሮፕላን ቅርጽ ሠርተው ወደ ነፋሱ ይለቁታል ፣ በዚያም ይረካሉ ። በውስጣችን ያለውን ነገር ለማውጣት መሞከር ያስፈልጋል ። በእያንዳንዳችን ውስጥ የተቀመጠ ውድ ስጦታ አለ ። ለመሞከር የሰዎችን ነቀፋ መፍራት ፣ እወድቃለሁ ብሎ መስጋት የለብንም ። ብዙ ውድቀቶች አንድ ትንሣኤ ይወጣቸዋል ። ደግሞም አለመሞከር እንጂ አለመሳካት አያጸጽትም። “ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃልና፥ ይነሣማል” (ምሳ. 24፡16) የስኬት ታሪክ የሚጻፈው በተደጋጋሚ የውድቀት ገጾች ላይ ነው! ከሞከርህ ታሳካለህ ፣ ካላሳካህ ትማራለህ ! ውድቀት የሙከራ ፈተና እንጂ የትምህርት ቤቱ የመልቀቂያ ፈተና አይደለም !
ተፈጸመ
ጥቅምት 12 ቀን 2019 ዓ.ም.