ዝና በሁለት መንገድ ይመጣል ። የመጀመሪያው ሊደበቅ በማይችል በጎነት ፣ ሙያ ፣ ድል አድራጊነት ፣ ለወገን በተከፈለ ዋጋ የሚመጣ ዝና አለ ። ሰውዬው ወደ ዝና የሄደ ሳይሆን ዝናው ራሱ ፈልጎት የመጣ ነው ። እንዲህ ዓይነት ዝና ሲመጣ መከልከል አይቻልም ። በልብ ላይ የሚነሣውን ትዕቢት ግን መገሠጽ ይቻላል ። ያከበረ ዓለም ቀጥሎ ማዋረድም ይችላልና ጥንቃቄ ያስፈልጋል ። ዝና ግሎ ሲመጣ መደበቅ ፣ መጸለይ ፣ አክብረህ አታውርደኝ ብሎ መማጸን ይገባል ። ከብርሃን ቀጥሎ ጨለማ እንደሚመጣ ከምስጋና ቀጥሎ ርግማን ይመጣልና መዘጋጀት መልካም ነው ። መፍራት ያለብን ዓለም ስትንቀን አይደለም ፣ ምክንያቱም ቆይታ ታከብረናለችና ። ዓለም በጠዋቱ ካደነቀችን ምሽቱ የውርደት ሊሆን ይችላል ። እንደ ተከበረ የፈጸመ ሰው በዓለም ላይ አይገኝም ።
ሁለተኛው ዝና የሚመጣበት መንገድ ወደ ዝና በመሮጥ ነው ። እነዚህ ሰዎች የሚታወቁበት በጎነትና ጀግንነት ሲያጡ በነውር ፣ በግፍ የበላይነትን ለመያዝ ፣ ርእስ ለመሆን ይፈልጋሉ ። ብዙ አሸባሪዎች የሃይማኖት ፣ የፖለቲካ ፣ የገንዘብ መሻት ሳይሆን የዝና ጥማት ያለባቸው እንደሆኑ ይታወቃል ። በሚሠሩት ግፍ ዓለም ስለ እነርሱ ሲያወራ በውስጣቸው የሚያሰቃያቸው የትንሽነት ሕመም ይታገሥላቸዋል ። የተረሱ ሲመስላቸው በሌላ ግፍ ብቅ ይላሉ ። ዝናና ታይታን ፍለጋ ወንጀለኛ ፣ ሃይማኖት አልባ ፣ ባሕል አስነዋሪ ሊያደርግ ይችላል ። ዝና ፣ ዜና ፣ ወሬ ማለት ነው ። ሰዎች በአፋቸው እኛን እንደ ቆሎ ሲያደቁን መደሰት የሚገርም ፍላጎት ነው ። በዚህ ዓለም ላይ ለመሰንበት በትንሹ መረሳት መልካም ነው ።
ሰዎች የታይታ ጥማታቸውን በእግዚአብሔር ቤትም ለመወጣት ይፈልጋሉ ። ለሚታወቁ ሰዎች በጎ በማድረግ ፣ ከታዋቂ ሰባኪያን ጋር በመገባበዝ ታይታን ይፈልጋሉ ። አንዱ ዝና አለው ፣ አንደኛው ገንዘብ አለው ። ገንዘብ ያለው ዝና ያለውን እየቸረ ዝነኛ ለመሆን ፣ የዝና ፍርፋሪ ለማግኘት ይፈልጋል ። የከተማው አብያተ ክርስቲያናት በገንዘብ ተጨንቀው ካህናቱን የወጠሩት ለገጠሩ የሚሰጥ ሰው ስለሌለ ነው ። የከተማው አብያተ ክርስቲያናት ላይ መስጠት ስምን ጎላ አድርጎ ያስነሣል ። ለታወቁ አገልግሎቶች መባ መስጠት በአደባባይ ማስታወቂያ ያስነግራል ። እውነተኛ ምእመን ታዋቂን ሳይሆን አዋቂን ፣ ዝነኛን ሳይሆን የተገፋውን አገልጋይ ይደግፋል ። የዚህ ዋጋው ያለው ከሥላሴ ዘንድ ብቻ ነው ። የምናደርገውን ሁሉ ለእግዚአብሔር ክብር ስናደርገው ደስታና የልብ ዕረፍት ይሰማናል ። እንኳን የምንሰጠው ገንዘብ ራሳችንም የእኛ አይደለንም ። ብሩ የእኔ ነው ብንል እንኳ እጁ እኔ የፈጠርኩት ነው በማለት መለኮት መልስ ይሰጠናል ። ይልቁንም ከአንድ አገልጋይ ጋር ለአገልግሎት መቆም መቻል መታደልና መመረጥ መሆኑን ማወቅ አለብን ። የሰራፕታዋ መበለት ነቢዩ ኤልያስን በቤትዋ ተቀብላ የረሀቡን ዘመን ሸሸገችው ። ንጉሡ ለሞት የሚፈልገውን ነቢይ መሸሸግ ዋጋ ያስከፍላል ። ይህች ሴት ግን እምነትዋ ትልቅ በመሆኑ እስከ ዛሬ ድረስ ታሪክዋ ይወሳል ። ለታሪኬ ብላ አልሠራችውምና ይኸው ስትነሣ ትውላለች ። ሴቶች ከተራቡ አገልጋዮች ጋር በመቆም ከጥንት እስከ ዛሬ ድረስ የእግዚአብሔርን ልብ አሳርፈዋል ። አቅሙ ያላቸው ወንዶች ግን ጨካኞች በመሆን የእግዚአብሔርን ልብ ያሳዝናሉ ።
ለእግዚአብሔር የምንሰጠው አሥራትና በኵራት ከፀጉር ወጪአችን ፣ ከቅባት ግዢአችን አንጻር ሲታይ በጣም ትንሽ ነው ። ለጉራ ብለን ከበር መልስ ሰዎችን የምንጋብዘው ከምንሰጠው አሥራት በመቶ እጥፍ የሚበልጥ ነው ። ታዲያ ያነሰ ስጦታ ሁሉን ለሰጠን ለእግዚአብሔር ሰጥተን በዚያ ታይታን መፈለግ ተገቢ አይደለም ። በርግጥ የአሥራት ስጦታ የተደነገገ በመሆኑ በግልጽም በድብቅም ቢያደርጉት አያስነቅፍም ። ስጦታችን ግን በስውር መሆን ያለበት ለራሳችን ጥቅም ነው ። ይህን ወደ ኋላ በደንብ እናየዋለን ። ለእግዚአብሔር ቤት የምንሰጠው ስጦታ ስሙ “የእግዚአብሔር ገንዘብ” የሚል ነው ። ይህ ሁለት ነገሮችን ይከላከላል ። የመጀመሪያው የእግዚአብሔር ገንዘብ ነውና ሰጠሁ ብሎ ሰጪውን አያስመካም ። ሁለተኛው ተቀባዩ አገልጋይ የእግዚአብሔር ገንዘብ ነውና ተቀበልሁ ብሎ አይሳቀቅም ። በዛሬው ዘመን እኛ በምንሰጣቸው ገንዘብ ነው የጠገቡት ፣ ገንዘባችንን ብናቆም አገልጋዮች ልክ ይገባሉ የሚል ንግግር ይሰተዋላል ። አሥራትን ገንዘቤ ማለት አሥራት ካለ ማውጣት እኩል ኃጢአት ነው ። ሠርተን ሠርተን ማበላሸት በእውነት አለመታደል ነው ።
ለድሀ አንድ ሚሪንዳ የሚያጠጡ ወጣቶች ያንን ለሚሊየን ሰው ያሳዩታል ። የሚያስደስታቸው ከስጦታው በላይ በሰዎች መታየት ነው ። ይህ ሁለት ጉዳት አለው ። የመጀመሪያው ለራሳቸው እርካታ አላደረጉትምና ደስተኛ አይደሉም ፣ በሰው ችግርም ነጋዴ ሆነዋልና ነፍሰ ገዳይ ናቸው ። ሁለተኛው ያጠጡትን ሰው አላረኩትም ፣ እርሱ ሳያወራው እነርሱ አውርተዋልና ። ወገኖቼ እየከፈልን ለመኰነን የበቃነው እንዴት ነው ? ኃጢአት ከመሥራት በላይ ጽድቁን ለራስ ክብር መጠቀም የበለጠ ኃጢአት ነው ። ደግሞስ አክብሮ ከሚያዋርድ ፣ በአንቱ ጀምሮ በአንተ ከሚጨርስ ትውልድ ክብር መፈለግ ቀኑን አለማወቅ ነው ።
ይቀጥላል
ኅዳር 4 ቀን 2019 ዓ.ም.