መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » የታይታ ጥማት » የታይታ ጥማት -4

የትምህርቱ ርዕስ | የታይታ ጥማት -4

ሰውየው ከሥር መቀመጫውን አራቁቶ በአናቱ ላይ ጋቢውን ጣል አድርጓል ። የሚሻለው መቀመጫውን መሸፈን ነበር ። እርሱ ግን እንደ ባላባቶች ከአናቱ ላይ ጣል አድርጎ በጉራ ቆሟል ። ሰዎችም የሥሩን ሳትሸፍን አናትህ ላይ ያደረግኸው ይህ ምንድነው ? ቢሉት “ወጉሳ ማዕረጉሳ” አለ ይባላል ። መሸፈን የሚገባውን ገልጠን ፣ መሸፈን የማይገባውን የምንሸፍነው የታይታ ኑሮ ስላለብን ነው ። የምንበላውና የምንጠጣው ለራሳችን ቢሆንም የምንኖረው ግን ለጎረቤታችን ነው ። በዚያ ዘመን በቤት ውስጥ መጋረጃ ማድረግ ፣ መኝታንም በዚያ መንጦላዕት መሸፈን እንደ ሀብት መለኪያ ይቆጠር ነበር ፣ ከሚለብሱት ተርፏቸው ጋርደዋል ይባልላቸዋል ። ታዲያ ባልና ሚስት ዕርቃናቸውን እያደሩ መጋረጃ ይጋርዱ ነበር  ። ባለጠጋ ለመባል ብለው ብርድ ይገርፋቸው ነበር ። ከሆንነው የምንባለው ያሳስበናል ። ሀብታም ቢሉን ሀብታም አንሆንም ፣ ድሀ ቢሉንም ድሀ አንሆንም ። የምንሆነው  የሆነውን ነው ። ኑሮው የእኛ ሳለ ጆሮአችን ግን ደጅ ያድራል ። በአጉል መግደርደርም ማደጋችን ይዘገያል ። ዛሬም የምንጨነቀው ባለጠጋ የሆነች አገርን ለመሥራት ሳይሆን ባለጠጋ የምትመስል አገርን ለማሳየት ነው ። ነዋሪዎቹ ጎብኚዎች እስኪመስሉን የምንኖረው ለውጭ ዜጎች ነው ። የራሳችንን እያዋረድን የሌላውን ብናከብርም ይታዘቡናል እንጂ አይቀበሉንም ።

ሁልጊዜ ደጃፋቸው ላይ ነጭ ጤፍ የሚያሰጡ ፣ እቤታቸው ግን ጥቁር ጤፍ የሚበሉ በብዛት ነበሩ ። ድሀ የያዘው ሁሉ ሀብታምን ስለሚያምር ዛሬ ላይ ጥቁር ጤፍ በባለጠጋው ቤት ገብቷል ። በቤታቸው የሚበሉት ነጭ ጤፍ ነው ለመባል የማይፈጭ እህል በየቀኑ ማስጣት የአካልም የአእምሮም ሥራ ነው ። ከገቢያችን ያልተመጣጠነ ወጪ የምናወጣው የታይታ ሰዎች ስለሆንን ነው ። ተበድረን እንጋብዛለን ፣ ሰላማችንን አስይዘን ገንዘባችንን እንበትናለን ። የሰጠነውንም አንረሳም ፣ የተጣላን ቀን የእኔ ውለታ ይህ ነው ወይ ? ብለን እናውካለን ። በዕለት ማስታወሻችን ላይ ውሎአችንን እንጽፋለን ፣ ይህ መልካም ነው ። የሰጠነውን ግን መርሳት እንጂ መመዝገብ የለብንም ። መስጠት የእግዚአብሔር ጠባይ ነው ፣ ስንሰጥ እርሱን እንመስላለን ። ሰጪና ተቀባይን ተጠቃሚ የሚያደርግ ግን በስውር ሲሰጥ ነው ። “አንተ ግን ምጽዋት ስታደርግ ምጽዋትህ በስውር እንዲሆን ቀኝህ የምትሠራውን ግራህ አትወቅ ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል” የተባለውን ማክበር አለብን ። (ማቴ. 6፡3-4) ። ቀኝና ግራ በጣም የተቀራረቡ ናቸው ፣ ስጦታህን የቅርብ ሰውም ትዳርህም ፣ ልጆችህም ቢሆኑ አይወቁ ማለት ነው ። ቀኝና ግራ ተጋግዘው ይሠራሉ ፣ አብሮ የሚሠራ ባልደረባህም አይወቅ ማለት ነው ። እንደ ስጦታ ጠላት የሚገዛ የለምና በስውር ማድረግ ተገቢ ነው !

የምናደርገውን በጎ ሥራ በመርሑ እንጂ በሰዎች ምላሽ መለካት የለብንም ። ታይታ እውነትን አይኮራባትም ፣ የገዛ ፍላጎቱንም አይከተልም ፤ ሁልጊዜ ሰዎች ለሚሰጡት አስተያየት ብቻ ጥገኛ ይሆናል ። በማኅበራዊ ሚዲያው የላይክና የሼር ምጽዋተኛ ይሆናል ። ታይታ የበላይነትን ለማስከበር የሚደረግ የበታችነት ስቃይ ነው ። በራስ እርግጠኛ አለመሆንና ሰዎች ካላዩን አለመሮጥ ነው ። የታይታ ጥማት ማስታወቂያን መውደድ ፣ የሰማይን ዋጋ መርሳትና ነጋዴነት ነው ። ዕቃ ይሸጣል ፣ ሰው እንዴት ራሱን ይሸጣል ? ለሰዎች ምስጋና ጥገኞች ከሆንን ካላደነቁን ሥራችን የተበላሸ መስሎ ይሰማናል ። እውነተኛ ባለ ራእይ ግን ሰው ባያየውም የሚሮጥ ነው ።

ይቀጥላል
ቅዳሜ ኅዳር 5 ቀን 2019 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ