“ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና። በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል”
/ዮሐ. 3፡17-18/።
የእግዚአብሔር ቃል በእያንዳንዱ ቊጥር ላይ አብረቅራቂ አልማዝ ነው። እጅግ ረቂቅ ነው ። ታሪኩም ፣ ፍልስፍናውም ፣ ሥነ ልቡናውም ቅዱስ ነው ። የእግዚአብሔር ቃል ሰፈፍ የሌለው ወለላ ፣ ገለባ የሌለው ፍሬ ፣ ግርድ የሌለው ምርት ፣ ነቊጥ የሌለው ጽሩይ ነው ። ከእግዚአብሔር ቃል የምንጥለው ምንም ነገር የለም ። ምግብ አንዳንድ ጊዜ በልተነው ይጣላናል ። ወደነው ብንበላውም ሕመም ይሆንብናል ። የእግዚአብሔር ቃል ግን ልንጣላው እንጂ ሊጣላን አይችልም ። የእግዚአብሔር ቃል መልክአ ሥላሴ ነው ፣ የአግዚአብሔርን መልክ የሚያሳየን ነው ። እግዚአብሔር ማለት እኛ እንዲሆንልን የፈለግነው ሳይሆን ራሱ ራሱን የሆነው እግዚአብሔር ነው ። እግዚአብሔርን በቃሉ ማወቅ ቀዳሚው ነገር ነው ። የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነውና ሰው ማወቁ የሚታወቀው ፈሪሃ እግዚአብሔር ሲኖረው ነው ። ከዚህ ቅዱስ ፍርሃት ውስጥ ፍቅር ይመነጫል ። ከዚህ ፍቅር ውስጥም እምነት ይመጣል ። ስለዚህ ሰው በመጣ ቀን አያምንም ማለት ነው። በመጣ ቀን ግማሹ ጓደኛውን ግማሹ እጮኛውን ፈልጎ የመጣ ነው ። ሳኦል አህያ ፈልጎ መጥቶ ንግሥና ይዞ እንደ ተመለሰ ሰውና ቊሳቊስ ፈልጎ የመጣም እግዚአብሔርን ይዞ ይመለሳል ። ስለዚህ በቤቱ የሚቀበለን ማመናችን ሳይሆን እግዚአብሔር ታማኝ መሆኑ ነው ። የእኛ ፍቅር አንዳንዶችን የሚመለከት ነው ። የእግዚአብሔር ፍቅር ግን ዓለሙን በሙሉ አድራሻ ያደረገ ነው ።
መዳናችን ትልቅ ዋጋ የተከፈለበት ነው ። የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ የሆነበት፣ የውርደት ሞት ለእኛ የሞተበት ነው ። ብዙ የምናከብራቸው የነጻነትና የድል ታሪኮች አሉ ፣ የክርስቶስ ሞት ከእነዚህ እንዳያንስብን መጠንቀቅ ያስፈልገናል ።
በእርሱ የሚያምኑ የዘላለም ሕይወት እንደሚያገኙ ተነግሯል ። የዘላለም ሕይወት የመጨረሻው ስጦታ ነው ። እግዚአብሔር የተወዳጀን የመጨረሻውን ሰጥቶን ነው ። የሰው ፍቅር አዳጊ በመሆኑ የክርስቶስ ፍቅር ሊያስደነግጠው ይችላል ። የዘላለም ሕይወት ማለት ዘላለም መቆየት ብቻ ሳይሆን ሞት የማያሸንፈው ህልውና ማግኘት ነው ። የዘላለም ሕይወት የሞትና የሲኦልን ኃይል የሚሽር ነው ። ዛሬ ከመሬት ባሻገር ስላሉ ነገሮች አሰሳ ይደረጋል ። ከሞት ባሻገር ስላለው ማንም አያጠናም ። ያ ክርስቶስን በማመን የሚገኝ ነው ።
– ሁሉም ስለ ተራራው ይናገራል ።
– ባለ ራእይ ከተራራው ጀርባ ስላለው መስክ ይናገራል።
– ከሞት ጀርባ ስላለው ክርስቶስ ብቻ ተስፋ ይሰጣል ።
ሩጫ ስንጀምር ከጀመርንበት ተቆጥሮ በፍጻሜው እንሸለማለን ። የዘላለም ሕይወትም ካመንበት ቀን አንሥቶ የሚጀምር ነው ። የዘላለም ሕይወት ግን የሩጫው መጨረሻ ሽልማት ሳይሆን የሩጫው ማስጀመሪያ ኃይል ነው ። የዘላለም ሕይወት የዘላለም ፍቅር ፣ የዘላለም ኅብረት ማለት ነው ። ወደ ሰማይ ከመሄዳችን በፊት ሰማይ ወደ ሕይወታችን መምጣት አለባት ። በሰማይ የሚቀጥል እንጂ የሚጀምር ነገር የለም ። የሰማይ ግብዣችን ዛሬ የምንካፈለው ፍቅርና ኅብረት ነው ። ነገር ግን ፍቅሩም ሆነ ኅብረቱም ፍጹም አይደለም ። ፍጹም አለመሆኑ ሰማይን እንድንናፍቅ ያደርገናል ። ፍጹም ነገር በዓለም ላይ የለም ። ፍጹም ነገር ብናገኝ እንኳ እኛ አባል ስንሆንበት ፍጹምነቱ ያበቃል ። ምክንያቱም እኛ ራሳችን ጎዶሎዎች ነንና ። ያለ ዘላለም ሕይወት ተስፋ ክርስትና አይጀመርም። ብዙ ቃል ኪዳኖች ቢኖሩም አዲስ ኪዳን ግን ከሁሉ ይበልጣል። ምክንያቱም የዘላለም ሕይወትን ይሰጣልና።
ክርስቶስ የመጣው እንዳንጠፋ ነው ። መጥፋት መደምሰስ አይደለም ። ኵነኔ ማለትም ተፈጥሮ እንዳልተፈጠረ መሆን ማለት አይደለም ። መጥፋት ከባለቤቱ እጅ ወጥቶ በሌባ እጅ መውደቅ ነው ። ዛሬ ገንዘብ ቢሰረቅብን ለእኛ የወር ወጪ ሲሆን ለሌባው ግን የቀን ወጪ ነው ። ባለቤት አይደለምና ያድፋፋዋል ። መጥፋት ማለት በጠላት እጅ መድፋፋት ነው ። ክርስቶስ ግን የመጣው ለዘላለም እንድንበረክት ነው ። ሰዎች ስጦታ ሲሰጡን ስጦታነቱ ለእኛ ሲሆን ክፍያው ግን ለእነርሱ ሆኖ ነው ። ማንኛውም ነጻ ስጦታ እዚያ ጋ ክፍያ አለው ። እግዚአብሔርም የዘላለም ሕይወትን ሲሰጠን ፍቅሩን ከፍሎበት ነው ። የዘላለም ጌታ የሞተው የዘላለም ሕይወትን ሊሰጠን ነው ። አንድ በሞት አፋፍ ላይ ያለ ሰው ቢድን እንደነቃለን፣ መሞት የሚገባው በመዳኑ ሐኪሞች ሳይቀር ከእውቀታችን በላይ ነው ይላሉ ። መሞት የሚገባው መዳኑ ሲያስደንቅ መሞት የማይገባው ክርስቶስ መሞቱ ግን ከሁሉ በላይ ያስገርማል ። እኛ ለቤት ሠራተኛችን ደም ለመለገስ እንኳ ፈቃደኛ አይደለንም ። እንኳን ልጃችንን የልጃችንን ልብስ መስጠት አንሻም ። እኛ ለበደለን ሰው የምናደርግለት የመጨረሻው ደግነት ህልውናውን መርሳት ነው። ጌታ ግን ለበደለው ሰው ሞተ ። በፍቅሩ ፊት ፍቅራችን ወራዳ ነው ። በሞቱ ያገለገለንን በጊዜያችን ማገልገል አቅቶናል ። በደሙ ሰላም የሰጠንን ጌታ ዛሬ ቤቱን በነገር እናምስበታለን ። እግዚአብሔር አብ ሕያው ቃሉን ወይም ልጁን እስከ ዛሬ ሙት የሚል ትእዛዝ አልሰጠውም ነበር ። ቃለ አብ ኢየሱስ ለልዩ ትእዛዝ ታዘዘ ። የላከ አብ ቡሩክ ነው ፣ የተላከም ወልድ ቡሩክ ነው ፣ ያሰመረ መንፈስ ቅዱስም ቡሩክ ነው ።
አንድ ልጅ እንኳን ለሞት ለማየትም ያሳሳል ። እግዚአብሔር ግን ልጁን ለሞት አሳልፎ ሰጠ ። ከባዱ ነገር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ መሞቱ እንጂ እኛ ስለ እርሱ መዳናችን አይደለም ። መንግሥተ ሰማያትን ቢቸረን ታላቅ ባለጠጋ ስለሆነ ነው ። ልጁን ቢሰጠን ግን እግዚአብሔር ፍቅር ስለሆነ ነው ። ተራራ ከሩቅ ይታያል ፣ ሥሩ ስንቆም ግን አይታይም ። ዛሬ በእግዚአብሔር ቤት ስላለን ያገኘነው ከፍታና ጸጋ አይታየንም ይሆናል ። ሌሎች ግን ከሩቅ ያዩታል ። አንድን ሰው ልባችንን ካልሰጠነው ቊልፋችንን አንሰጠውም ። የሚበልጠውን ልብ ካገኘ በኋላ የሚያንሰውን ቊልፍ ያገኛል። እግዚአብሔርም ከሁሉ በላይ የሚሆነውን አንዱን ልጁን ሰጠን ። የልቡን መልእክተኛ ልጁን የሰጠ ጸጋውንና መንግሥቱን እንደሚሰጥ እርግጥ ነው ። እምነት በእግዚአብሔር መደላደል ነው ። ለዘላለሙ ያመነውን እግዚአብሔር ለጊዜያዊ ጉዳይ እንዴት እንፈራዋለን? ማመን ቀላል አይደለም ፤ ላመነ ሥራ ቀላል ነው ። እምነት በሌለን ነገር ማረፍ ሲሆን ምግባር ደግሞ ባለን ነገር መሥራት ነው ። ብዙ የምንወደው ሰው ሊኖር ይችላል ፣ የምናምነው ግን ጥቂት ነው ። ማመን በእኛ ፍቅር ብቻ ሳይሆን ሌሎች ለእኛ ባላቸው ፍቅርም እርግጠኛ መሆን ነው ። ይህንን መታመን ሊሸከም የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው ።
“ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና። በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል” ይላል /ዮሐ. 3፡17-18/። ባሉበት ቦታ የሚወረወር ቀስት እርሱ ፍርድ ነው ። ሰውዬው ካለበት ድረስ የሚሄድ ግን ፍቅር ነው ። ሰውዬው በሌለበት ፍርዱ ይታያል። ፍቅር ግን ሰውዬውን ማግኘት ይፈልጋል ። ለፍርድ ዙፋን ሲያስፈልግ ፣ ለፍቅር ግን በረትና መስቀል አስፈላጊ ሆነ ። እግዚአብሔር ዓለሙን ሁሉ ሊቀጣ ቢፈልግ በዙፋን ልዕልናው ሆኖ መቅጣት ይችል ነበር ። የበረት ትሕትናው ግን ለመዳን የተከፈለ ዋጋ ነው ። ልዕልና ይፈርዳል ፣ ትሕትና ግን ከውድቀት ሥር ገብቶ የጠለቀውን ሰው ያድናል ። አንድ በውኃ ውስጥ የሰጠመን ሰው ለማዳን እርሱ ባለበት ውድቀት ልክ መሆን አይበቃል ። ከእርሱ ውድቀት በታች መሆን ያስፈልጋል ። እግዚአብሔር ወልድም ያለ ልክ ተዋረደ ። እግዚአብሔር ዓለሙን ቢፈርድበት ሕጋዊ ነበር፣ ዓለሙን በማዳኑ ግን መሐሪ ነው ። እኛም ባሕርዩን ተካፍለናልና ፍቅርም ፍርድም አለን ። ሁለቱም ያለው እግዚአብሔር ግን ፍቅርን አስቀደመ ። ፍርድን በሚመለከት እግዚአብሔር የሚርቀው ግዛት የለም ። የጌታችን ዓላማ ግን መፍረድ ሳይሆን ማዳን ነው ። እግዚአብሔር የመፍረድ ሥልጣኑን ቢጠቀም መላው ዓለም እስር ቤት ፣ መላው የሰው ዘር እስረኛ ይሆን ነበር ። አሳሪው ሁሉ አብሮ ታሳሪ ፣ ፈራጁ ሁሉ ራሱ ፍርደኛ ይሆን ነበር ። ማዳን የእግዚአብሔር ነው ። በእግዚአብሔርነት ሥልጣን የሚፈጸም ነው ። ማዳን ትልቅ ተግባር ነው ። በእውነት እግዚአብሔር እስር ቤቶችን ሲያይ ምን ይል ይሆን ? በእርሱ ቅድስና ፊት የማይታሰር የለምና ። አዎ ማዳን ሰውዬው ያለበት ድረስ መሄድን ይጠይቃል ፣ መደበኛ በሽታዎች በሐኪም ቤት ይታከማሉ ፣ ወረርሽኝ ግን በሽተኞቹ ያሉበት ድረስ መሄድ ይፈልጋል ። አዳምንና ዘሩን የበከለውን የኃጢአት ወረርሽኝ ለማዳን ራሱ ሐኪም ራሱም መድኃኒት ሁኖ ጌታችን መጣ ።
አዎ ጌታችን የመዳን ጽኑ ምክንያት እንደሆነ ሁሉ የኵነኔም ጽኑ ምክንያት ነው። ወይ ጥያቄአችን ወይ መልሳችን ነው ። ከእርሱ ጋር በምሕረት ካልተገናኘን በፍርድ መገናኘታችን ግድ ነው ። በእርሱ የሚያምን ግን አይፈረድበትም ። ሲያምን ዕዳው የተከፈለበትን ደረሰኝ ስለሚቀበል ነው። ጌታችን ጋ ስንመጣ ስለ ኃጢአታችን ይጠየቅልናል ፣ ራሳችን ጋ ስንሆን በኃጢአታችን እንጠየቃለን ። እምነት ማለት ከኃጢአቴ ይልቅ ማመኔ ያስመልጠኛል ብሎ መተማመን ነው ። ማንም ሊያስውል ይችላል ፣ ሁሉም ግን አያሳድርም ። በቀን የሚያምኑትን በጨለማ አያምኑትም ። ከቤት የተጣላ ልጅ ቀን ላይ ረስቶት ይውልና ሲመሽ ግን መጨነቅ ይጀምራል ። ታዲያ የእናቱና የአባቱ ጽኑ ወዳጅ የሆኑት ሰው ደጅ ላይ ያንዣብባል ። እነርሱም ምን ሆነሃል? ብለው ይጠይቃሉ ። ልጁም መጣላቱንና ለመመለስ ድፍረት ማጣቱን ከገለጠ በኋላ ይዘውት ወደ ወጣበት ቤቱ ይመጣሉ ። ታዲያ እኒያ አስታራቂ እናት ልጁን ከኋላ በቀሚሳቸው ከልለው ለቊጣው ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተው ይገባሉ ። የተበሳጨው ወላጅም ብዙ ቊጣውን ያወርዳል። ሲጨርስ አስታራቂዋ እናት “ስለ እኔ ብላችሁ ተቀበሉት ፣ በሞቴ ፣ እኔ እክሳለሁ” ብለው ይማለላሉ ። ስለ ማንነቱ ሳይሆን ስለቀደመለት ወዳጅ ያ ልጅ ይመለሳል። ኢየሱስም ቀን የጨለመብንን የእኛን ቊጣ ተሸክሞ እኛን በጽድቅ ከልሎ አስገባን ። ያ ልጅ ከወላጁ ቅጣት ይዞት በመጣው ሰው ምሕረት ያምናል ። ማመን ቀላል ሳይሆን ብርቱና አስደሳች ነገር ነው ። ታዲያ እኒያ ቊጣችንን የተሸከሙልን እናት ከእናታችን በክብር የሚያንሱ አይደሉም ። እኩያ ናቸው ። ኢየሱስም ቊጣችንን በመሸከሙ ከአባቱ አያንስም እንደውም እኩያ ነው ። እኩያ ባይሆን ሕርቁም ባልተገኘ ነበር ።
በእርሱ የማያምን አሁን ተፈርዶበታል ይላል ። የሚያምን ደግሞ አሁን ከኵነኔ ድኗል ። ጳውሎስ ሐዋርያ ፡- “እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም” ይላል /ሮሜ . 8፡1/። በጌታ ቀኝ የተሰቀለው ወንበዴ እንደ ሰው ሁሉ የእኔ ዕጣ የሚለው በምጽአት ቀን ነው ብሎ ያስብ ነበር ። ስለዚህ ፡- “ጌታ ሆይ፥ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ አለው። ኢየሱስም፦ እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ አለው” /ሉቃ .23፡42-43/። ጌታችን አርሞ ሰማው ። እምነት አሁን ነው ።