“…ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ ፥ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ ።” ሉቃ. 1 ፡ 27 ።
የማርያም ስሞች
ድንግል
ለእመቤታችን ከተሰጡ ስሞች አንዱ ድንግል የሚለው የንጽሕናዋ መግለጫ ነው ። ወንድን ካለማወቅ ብቻ ሳይሆን ከኃጢአትም ድንግል መሆንዋን የሚያመለክት ነው ። በሁለት ወገን ድንግል የሆነች ናት ። እንኳን አምላክን የወለደች ፣ አምላክን የወደደች ነፍስም ዘመንዋ ለእግዚአብሔር የተሰጠ ፣ ሕሊናዋ በደመ ኢየሱስ የተረጨ ነው ። ድንግል የሚለው መጠሪያ ክብርን ያመለክታል ። በአንዲት ወጣት ድንግልና ቤተ ዘመድ ይኮራል ። በድንግልና ያለች ሕሊናዋ ያልባከነ ፣ ለዓላማ የተዘጋጀች ፣ የአንድ ሰው ብቻ ለመሆን የምትጠብቅ ናት ። ከጥንት ጀምሮ እስካሁን ድረስ አይሁዳውያን መሢሑን ይጠብቃሉ ። የመጣውን ጌታ አሁንም አልተቀበሉትም ። ታዲያ ከአንድዋ ልጃችን ሊወለድ ይችላል ብለው እስከ አሥራ አምስት ዓመት ድረስ ልዩ ጥበቃ ያደርጉላታል ። አይሁዳውያን ድንግል የሆነች ልጃቸውን ለአንድ ወንድ በክብር ለመዳር ብቻ ሳይሆን ለመሢሑ እናት እንድትሆንም ይመኛሉ ። መሢሑን በየቤታቸው በልጃቸው ላይ ይጠባበቃሉ ። ከአሥራ አምስት ዓመት በኋላ ግን ለሌላ ወንድ ያጫሉ ። ድንግልና ትልቅ ክብር የሚሰጠው ነው ። ተፈጥሮአዊ በሆነው መንገድም በድንግልና የሚጋቡ በትዳር መጽናታቸው የተረጋገጠ ነው ። ድንግልና ራስዋ ወጣትዋና ቤተሰብዋ የትዳርን ክብር ለመጠበቅ ብለው የሚዘጋጁበት ነው ። አንዲት በድንግልና ያለች ሴት ቤተሰብዋን ታኮራለች ።
ገነትና ናዝሬት ይናበባሉ ። ሔዋን በገነት የኖረችው በድንግልና ነው ። ድንግል ወደምትሆን ሔዋን ሰይጣን መጣ ፣ ድንግል ወደምትሆን ወደ ማርያም መልአክ መጣ ፣ ድንግል ወደምትሆን ማርያም መልአክ መጣ ። ድንግል የምትሆን ሔዋን ቃሉን የሚያሳብል ምክር መጣላት ፣ ድንግል ማርያም ቃልን ሰምታ የቃል እናት ሆነች ። ድንግል የምትሆን ሔዋን ውዳሴ ከንቱን ተቀበለች ፣ ድንግል ማርያም ግን እውተነኛ ምስጋና በመጣላት ጊዜ “ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው?” ብላ መረመረች ። የማታስተውል ሔዋን ያልተሰጣትን ፈለገች ፣ አስተዋይ ማርያም የተሰጣትን በትሕትና ያዘች ፤ ሥራ ፈት ሆና ሔዋን ሞትን አመጣች ፣ በሥራ ላይ ሁና ድንግል ማርያም የዓለምን መዳን ሰማች ፤ ምሥጢርን ያሾለከችው ሔዋን የሰይጣን ባሪያ ሆነች ፣ ምሥጢርን የጠበቀችው ማርያም የወልድ እናት ሆነች ። ድንግል የምትሆን ሔዋን አምላክ መሆን ይገባኛል አለች ፣ ድንግል ማርያም የአምላክ እናት መሆን አይገባኝም አለች ። ድንግል በምትሆን የሔዋን ዘር ከገነት ወጣን ፣ ድንግል በምትሆን በማርያም ዘር ወደ ገነት ገባን ።
ድንግል የምትሆን ሔዋን የቀድሞ ስሟ ሴት ነበረ ፣ ድንግል ማርያምም ሴት ተብላ ተጠርታለች (ዘፍ. 3 ፡ 15 ፤ ገላ. 4 ፡ 4) ። ድንግል የምትሆን ሔዋን የኋላ ስሟ የሕያዋን እናት ወይም ሔዋን ሆነ ፣ ድንግል የምትሆን ማርያም በክርስቶስ አምነው ለዳኑ ለሕያዋን ሁሉ እናት ሆነች ።
አምላክ ከድንግል ሴት መወለድን ለምን መረጠ ? ብለን መጠየቅ አለብን ። ከወለደች ሴት ወደፊትም ሌሎች ልጆችን ከምትወልድ ሴት ለምን አልተወለደም ? ዘላለማዊት ድንግል ከምትሆን ከማርያም ለምን ተወለደ ? አምላክ በሚቀመጥበት ዙፋን ፍጡር መቀመጥ ስለማይችል ድንግል ከምትሆን ከማርያም ተወለደ ። ሉቃስ ወንጌሉን የጻፈው ከዕርገቱ በኋላ ነው ። ከዐርባ ዓመት በኋላ ድንግሊቱ እያለ ይጽፋል ። ድንግልና መዳረሻዋ ሳይሆን ሕይወትዋ ነውና ። ሥጋዊ ቤተሰቦች ለተለያየ ነገር ቢያጩአት አብ ግን ከሰማይ የልጁ እናት እንድትሆን መረጣት ። ሰማይና ምድር የማይችሉትን ጌታ በተሸከመች ጊዜም አብ አጸናት ። የወልድ ታላቅነት በታየን ቍጥር ምን ያህል ክብር እንዳላት እንረዳለን ። ጠላትን ስለ መውደድ በሚሰብክ ክርስትና ፣ ታናናሽን ስለ ማክበር በሚናገር እምነት ውስጥ ያለ ሰው ድንግል ማርያምን ሊጠላና ሊንቅ አይችልም ። ክርስቶስን የሚጠላ ሁሉ ድንግል ማርያምን ይጠላል ።
ድንግል የሚለው ስም እስከ ጊዜው ክብር ነው ። ለዘለቄታው ወደ ትዳር ያልገባች ሴት ግን በድንግልናዋ እያፈረች ፣ አልፈለግም በሚል ስሜት እየተጎዳች ትመጣለች ። ድንግል የሚለው መጠሪያ ቆይቶ ክብር አይሆንም ። ለቅድስት ማርያም ግን ድንግል መባል የክብር ስም ነው ። ከእርስዋ በድንግልና መወለዱ የአምላክነቱ አስረጂ ነውና በእውነት እናደንቃለን ።
ብዙ ሰዎች ወልዳለች ብለው ይናገራሉ ። መውለድ ጸጋ እንጂ ውርደት አይደለም ። ይህን ቃል የሚጠቀሙት ድንግል ማርያምን ያሳነሱ መስሎአቸው ነው ። ያልተሰጣት ሆኖ ከአንዱ ከክርስቶስ በቀር ልጅ የላትም ። እውነት ነው ብዙ ልጆች አሉአት መባሉ ምሥጢራዊ ነው ። በመስቀል ላይ ዮሐንስ ልጅ ሁኖ ተሰጣት ። ለድንግል ፣ ድንግል ዮሐንስ ልጅ ሆናት ። ከዚያ በኋላ በመስቀሉ ፍቅር ተማርከው በክርስቶስ ያመኑ ሁሉ ልጆችዋ ናቸው ። እናታችን ሣራ እያልን እናታችን ማርያም ማለት አያሳፍርም ። ደግሞም የአምላክ እናትን እናቴ ማለት ክብር ነው ።
ደናግላን ለቤተ ክርስቲያን አስፈላጊ ናቸው ። ሐዋርያዊ ተልእኮን ለመፈጸም ማቄን ጨርቄን የማይሉ ሠራተኞች ናቸው ። በብሉይ እነ ኤልያስ በሐዲስ እነ ዮሐንስ ወንጌላዊ ሞትን ሳያዩ የተሰወሩበት ጸጋ ነው ። ደናግላን እኛ ደረቅ ዛፍ ነን እንዳይሉ ድንግል የሕይወትን ፍሬ አፍርታለችና የደናግል መመኪያ ትባላለች (ኢሳ. 56፡1-7)።
ቀዳማዊ አዳም ያለ ዘር ከድንግል መሬት ተወለደ ፤ ዳግማዊ አዳም ክርስቶስ እንበለ ዘርአ ብእሲ ከማርያም ተወለደ ። ድንግል ማርያም ለመፅነስ ዘር ምክንያት አልሆናትም ። በሕይወታችን የሰው እርዳታ ፣ የመውጫ መሰላል ፣ የበረከት ምክንያት የሚሆን ምድራዊ ትምክሕት ባይኖረንም ያለ ደመና የሚያዘንብ ፣ ያለ ወንድ ዘር የተወለደው እርሱ ሥራችንን ይሠራልናል ። ምንም የለኝም ብለው ለሚፈሩ የድንግል ማርያም ጸጋ መመኪያ ይሆናቸዋል ። የእርስዋ በድንግልና መፅነስ እግዚአብሔር ሲሠራ ምክንያት አይሻም የሚል መልእክት አለው ፣ በድንግልና መኖርዋ እግዚአብሔር የሚጦር የሚደግፍ ልጅ መሆኑን ምስክር ነው ። ሁለት ነገሮች በድንግል ማርያም ላይ ተባብረዋል ። እናትነት ከድንግልና ።
ድንግል ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ ! ብዙ ልጆች ተወልደውልሻል !
ይቀጥላል
ነሐሴ 9 ቀን 2018 ዓ.ም.