ብዙ ሰው ወደ እግዚአብሔር መምጣት የሚፈልገው የሚሠራውን ኃጢአት ትቶ ፣ የሚያደርገውን ሱስ ጥሎ ነው ። ሕፃን ልጅ ወደ ወላጁ የሚሮጠው ከነ ቆሻሻው ነው ። የጠፋው ልጅም ታጥቦና ታጥኖ ወደ አባቱ አልመጣም ፣ ከነቆሻሻው መጣ ። አባቱም ተቀብሎ ነጩን ልብስ አለበሰው ። ብዙ መጠሪያዎች ሳሉት በአዲስ ኪዳን “አባታችን ሆይ” በሉኝ አለ ። ፍቅሩ ከምድር አባት ይበልጣልና “በሰማይ የምትኖር” ብላችሁ ጨምሩበት አለ ። ምድራዊ አባት አምሳል የማይሆነው ልዩ አባት ነው ። ሕፃን ልጅ ራሱን ማጽዳት አይችልም ፣ ስለዚህ ወደ ወላጆቹ ከነቆሻሻው ይሮጣል ። ሰውም ራሱን ከኃጢአት ማላቀቅ አይችልም ። ከነድካሙ ወደ እግዚአብሔር መምጣት አለበት ። መድኃኒት የሚያስፈልገው ለታመመ ነው ፣ ኃጢአትም ከጌታ እንድንርቅ ሳይሆን ይበልጥ እንድንቀርብ ሊያደርገን ይገባል ። እርሱ ብቻ ሸክማችንን ማውረድ ይችላል ። በሽታው ምክንያት ሁኖት ታማሚ ወደ ሐኪም እንዲመጣ ኃጢአታችንም ፈውስ ያስፈልገዋልና ወደ ክርስቶስ መምጣት ያስፈልገናል ። ለቀደመም ለዘገየም ፣ በጠዋት ለመጣም በሠርክ ለገባም የክርስቶስ በር ክፍት ነው ። በጊዜ መግባት ግን ከመባከንና ከማባከን ያድናል ። ወደ እግዚአብሔር የምንመጣው ኃጢአታችንን ጥለን ሳይሆን የተሰበረ ልብ ይዘን ነው ።
የጠፋው ልጅ ሁሉን ከስሮአል ። አባቱ ግን አባትነቱ የሚለወጥ አልነበረም ። ስለዚህም “ወደ አባቴ ቤት እሄዳለሁ” አለ (ሉቃ. 15፡18) ። ሦስት የተመረጡ ነገሮችን አደረገ፡- የመጀመሪያው በምርጫው ሁሉን እንደ ከሰረ ተገነዘበ ፤ ሁለተኛው፡- አባቱ አባትነቱ እንደማይለወጥ ተረዳ ፤ ሦስተኛ፡- ከነ ማንነቱ ወደ አባቱ መጣ ። ወላጅ ሕፃን ልጁን ቆሸሸ ብሎ አይጸየፍም ፣ እግዚአብሔርም ኃጢአተኞችን ጸድታችሁ ኑ አይልም ። ደካማና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ ብሏል ። ደካማነታችን ራሳችንን ንጹሕ ማድረግ አለመቻላችን ነው ። ሕፃን ልጅ ደካማ ቢሆንም የተወደደ ነው ። እግሮቹ በቅጡ አይራመዱም ፣ ትከሻው ሸክም አይችልም ፣ እጆቹ ለሥራ ያልደረሱ ስስ ናቸው ። ይህ ድካሙ ግን እንዲጠላ አላደረገውም ። በኃጢአታችን ምክንያት ከእግዚአብሔር ከመራቅ በኃጢአታችን ምክንያት ወደ እርሱ መቅረብ ይገባናል ። ምክንያቱም መታመሙን ያወቀ ከመድኃኒት አይርቅምና ።
ለሰው ልጅ መቆሸሽ መጨረሻው ቢሆን ኖሮ ከባድ ነበረ ። አብርሃምን አበ ብዙኃን ፣ ሙሴን ሊቀ ነቢያት ፣ ዳዊትን ልበ አምላክ ፣ ጴጥሮስና ጳውሎስን ብርሃናተ ዓለም ብለን ባልጠራን ነበረ ። እግዚአብሔር ታሪክን ይለውጣል ፣ የወደቀውን አንሥቶ የክብር ዕቃ ያደርገዋል ። ሕፃን ልጅ ቆሽሾ ንጹሕ ነኝ ብሎ አያስመስልም ። መቆሸሹን አምኖ ወደ ወላጆቹ ይመጣል ። ተሳስቻለሁ ማለትን አንወድም ። ሰውነት ፣ ሥልጣኔ ፣ መንፈሳዊነት ፣ ትልቅነት ፣ አዋቂነት ተሳስቻለሁ ብሎ ስህተትን ማመን ነው ። እንደ ሕዝብ የወደቅነው ተሳስቻለሁ ማለትን ባለ መውደድ ነው ። ስህተታችንን ከማመን ሚሊየኖች ቢያልቁ እንመርጣለን ። ያንንም እያደረግነው ነው ። በአገራችን የራስን ስህተት ከማመን በሌሎች ስህተት ውስጥ መደበቅ እንመርጣለን ። የሰውን በደል የሚያጮህ የራሱን ማሰብ የማይፈልግ ሰው ነው ። ሁለተኛው፡- በአገራችን የተበደለ ሰው ዝም ይላል ፣ በዳይ ግን እየዞረ ስሙን ያጠፋል ። የሚገርመው በዳዩን እያመኑ የተበደለውን እንደገና የሚጎዱ መብዛታቸው ነው ። በዳይ የሚዞረው ኃጢአቱ እያቅበዘበዘው ፣ ሕሊናው እየጮኸበት ነው ። ይቅርታ በማለት ከታላቅ ወጀብ መዳን ሲችል በየቀኑ ሲኦልን ተሸክሞ የሚዞር ብዙ ግፈኛ አለ ። ንስሐ የተዘጋጀው ለበደለ ሰው ነውና ወደ ክርስቶስ መቅረብን መፍራት የለብንም ። ሰዎች ይፈርዳሉ ፣ ክርስቶስ ግን ያድናል ።
ሰው የተሰረቀ ንብረቱን በትጋት ይፈልጋል ፣ የጠፋ በጉንም በምሽት ያስሳል ። ንብረቱን ለሌባ ፣ በጉን ለአውሬ የሚተዉ ደግ የለም ። እግዚአብሔርም ልጆቹን ለኃጢአትና ለበደል አይተውም ። ሲመሽ የሚፈልግ አምላክ ነው ። “እነርሱም ቀኑ በመሸ ጊዜ የእግዚአብሔርን የአምላክን ድምፅ ከገነት ውስጥ ሲመላለስ ሰሙ” ይላል ። (ዘፍ. 3 ፡ 8) ። ቀኑ ሲመሽ ፣ እንኳን አብሮ የዋለ ወዳጅ የገዛ ጥላም ይሰወራል ። የሥልጣን ፀሐይ ሲመሽ ሁሉም ሰው ድንጋይ አንሥቶ ይወግራል ። የሀብት ጀምበር ሲመሽ ሁሉም ሊሳደብ አፉን ያላቅቃል ። የጉልበት ጸዳል ሲመሽ ተናቅሁኝ ያለ ሁሉ ግብግብ ውስጥ ይገባል ። “ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል” እንዲሉ ። ተፈርዶብን ስንጋዝ ሁሉም ይገባዋል ይላል ። ስንሾም “ይደልዎ-ይገባዋል” ያለ ስንሻርም “ይደልዎ” ይላል ። የሚገባህ ሕይወት ነው የሚል የምሽት ፈላጊ እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ሕፃን ልጅ ሳይሳቀቅ ከነቆሻሻው ወደ አባቱ ይመጣል ፣ አባቱም ይቀበለዋል ። እግዚአብሔርም ከነቆሻሻችን ተቀብሎ ነጩን ልብስ የሚያለብሰን ልዩ አባታችን ነው ።
ሕፃን ልጅ የሚቆሽሸው እሠራ ብሎ ሳይሆን እጫወት ብሎ ነው ። ልብሱ ሸትቶ ፣ መልኩ ጠፍቶ ፣ ከነማንነቱ ወደ አባቱ ይሄዳል ። አባቱም ተቀብሎ መክሮ ያጸዳዋል ። እኛም እጫወት ብለን በኃጢአት ቆሽሸናል ፣ በበደል ተጎሳቁለናል ፣ መንፈሳዊ መልካችን ጠፍቶአል ። እግዚአብሔር ግን ወደ ቀደመ ክብራችን ሊመልሰን ሁልጊዜ ይጠብቀናል ። በኃጢአት መጫወት በፈንጂ ኳስ እንደ መጫወት ነው ። የደጅ ሰዎች ሕፃኑን ሊያቅፉትና ሊስሙት ሲሉ ወላጆች “ቆይ ቆሽሾአል” ብለው ሊያጥቡት ይወስዱታል ። ከነቆሻሻው ሊያቅፈው የሚችል ወላጅ ብቻ ነው ። ሌላው ሰው ፍቅሩ መስፈርት አለው ። ወላጅም ቢሆን ያጸዳል እንጂ ከልጁ ቆሻሻ ጋር ስምምነት አይፈራረምም ። እግዚአብሔር ለዘላለም ኃጢአተኞችን ይወዳል ፣ ለዘላለም ኃጢአትን ይጠላል ።
ይቀጥላል
መስከረም 28 ቀን 2019 ዓ.ም.