የትምህርቱ ርዕስ | ቀጥተኛነት

ልጆች ልጅነታችንን የምናይባቸው መስተዋቶች ናቸው ። የልጅነታችን ፈገግታ ፣ ደስታና ቡረቃ በልጆች ላይ እናየዋለን ። የጎዳንን ሰው እንደገና ስንቀርበው ፣ ከጉዳቱ ፍቅሩ ሲበልጥብን ልጅነታችንን እንገረምበታለን ። ወላጆቻችንን በጣም እንዳደከምናቸው ፣ ለእኛ ሲሉ ከብዙ ነገር እንደ ቀሩ ልጆችን ስናይ እናስተውላለን ። ጨርቃቸውን ይዘን አልለቃችሁም እያልን እንዳላለቀስን ዛሬ ስልክ እንኳ ሲደውሉ ማንሣት አለመፈለጋችን አስደናቂ ነው ። የሰፈሩን ሰው ሁሉ ዘመድ አድርገን እንዳላደግን የሰፈሩን ሰው ሁሉ ማኩረፋችን ፣ እንዲሁ የበቀልኩ ነኝ ለማለት ዳር ዳር ማለታችን በእውነት ዕድገት ነው ወይስ መቅረት እንድንል ያስገድዳል ። ልጆች ልጅነታችንን ያስታውሱታል ። ልጅነት ተመልሶ የማይመጣ ፣ የሕይወታችን ውብ ስጦታ ነው ። በዚያው ልክ ልጅነታቸው ትልቅ ትግል የሆነባቸው ፣ ከአንዱ ቤት ወደ አንዱ ቤት ተንከራተው ፣ ጉልበታቸው ተበዝብዞ ፣ ወላጅ አልባ ሁነው ፣ የወለደም ጨክኖባቸው በሐሣር ያደጉ አሉ  ። የወጡበት መሰላል የማያምር ቢሆንም እዚህ ስለ መድረሳቸው ብቻ ማመስገን አለባቸው ። ሊገድል በቂ የሆነው ችግር ሳይገድላቸው ከዚህ መድረሳቸው የምስጋና ርእስ ነው ። በልጅነታቸው የቤተሰብ ኃላፊነት የወደቀባቸው ትሑታን ፣ ሠራተኞችና ከዕድሜአቸው በላይ አሳቢ ፣ ትርፍ ነገር የማያምራቸው ፣ ራሳቸውን የገዙ ሁነዋል ። ቃሉም፡- “ሰው በታናሽነቱ ቀንበር ቢሸከም መልካም ነው ፤ እርሱ አሸክሞታልና ዝም ብሎ ለብቻው ይቀመጥ” ይላል ። (ሰቆቃ. 3 ፡ 27) ።

እግዚአብሔር ሁሉን ሲያደራጅ ያውቅበታል ። አንዳንዱ በጥሩ አድጎ በከባድ ትግል ያረጃል ። ሌላው ደግሞ ማለዳው ጨለማ ሆኖበት ማታው ብርሃን ይሆንለታል ። በልጅነቱ በበሽታ ሲንገላታ ያደገ ወደ ኋላ ጤነኛ ይሆናል ። በእንጀራ አባትና እናት ሲሰቃይ የኖረ የማታ እንጀራ አለው ። በሚወዳት እናቱና በማይወደው እንጀራ አባት ፣ በሚያፈቅረው አባቱና ለምን ተወለድህ ብላ በምትጠላው እንጀራ እናት መካከል ማደግ ሳይጠጡ ያሰክራል ። የአእምሮ መታወክ ገና በልጅነት የሚጀምር ጉዳት ነው ። ትልቅ ፍቅርንና ትልቅ ጥላቻን ፣ ምክንያት የሌለው ውድንና ምክንያት የሌለው መገፋትን ማስተናገድ ያደናግራል ። ያ ልጅ ከእገሌ እንዲወለድ አሳብ አላቀረበም ። ከስኬታችን ባላጋራዎች የመወለዳችን ጠላቶች ይከፋሉ ። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን የመኖር መብትን የሚሰጥ አንዱ አምላክ ብቻ መሆኑ ደስ ያሰኛል ።

ጊዜን ወደ ኋላ መመለስ አይቻልም ፣ ልጅነትም ተመልሶ አይመጣም ። ትዝታው ግን እስከ ሕይወት ዘመን ድረስ የመንፈስ ምግብ ነው ። ልጅ ሆኜ ደግ ነበርኩ ብሎ በጽድቁ የሚኮራ ፣ ክፉ ነበርሁ ብሎ በኃጢአቱ የሚሳቀቅ የለም ። ልጅነት ሁሉን ነገር አቅልሎ የሚመለከት ነው ። በልጅነት የተዘራብን ነገር እስከ ሽምግልና ይበቅላል ። የወደፊቱ ሕይወታችን የሚወሰነው ቤተሰብ ስለ ዓለም በነገረን ነገር ላይ ነው ። ከሁሉ በላይ የወላጆች የእርስ በርስ ፍቅርና ንትርክ የወደፊት ሕይወት ላይ ጥላ ያጠላል ። በምድር ላይ ጠብ እንደ ሕፃናት የሚረብሸው ማንም የለም ። ወላጁን የፈራ ልጅ ማንንም ማመን አይችልም ። ልጅነት ሰዓቱ ላይ ደስታ ፣ አልፎ ግን ትዝታ ነው ። የትላንቱ አሻራ ሲጠፋ የልጅነት ትዝታም አብሮ ይጠፋል ። የወላጅ ቤት እንዳይሸጥ የተወለዱት መትጋት አለባቸው ፣ ትዝታ አብሮ ይጠፋልና ! ከተማ ሲፈርስ ያደጉበትን ሰዎች ትዝታ እንዳንነካ ጥንቃቄ ይፈልጋል ! ዜጋ ባይተዋርነት ከተሰማው የቁም ሞትን ይገፋል !

ልጆች ቀጥተኛ ናቸው ። በሚናገሩትና በሚያስቡት መካከል ልዩነት የለም ። የሚወዱትን ሰው ከልብ ይወዱታል ፣ የሚጠሉት ሰው ሲመጣም አያስመስሉም ። እሪ ብለው ይጮኻሉ ። ትክክለኛ ነው በተባሉት መንገድ ላይ ቀጥ ብለው ይሄዳሉ ። የተነገራቸውን ከልብ ያምናሉ ። እግዚአብሔርንም አጠገባቸው እንዳለ አድርገው ያነጋግሩታል ። ወደ ግራ ወደ ቀኝ አለማለት ፣ በዘመን ፣ በሀብትና በሥልጣን ሰዓት አለመለዋወጥ የትልቅ ሰው ምልክት ነው ። ሁሉ ሄዶ የሚቀረው ሰውነት ነው ። ለሚያልፍ ቀን የማያልፍ ትዝብትን ላለማትረፍ ጠንቃቃ መሆን ይገባል ። አቋምን ሲለዋውጡ መኖር ተገቢ አይደለም ። ለምናምነው ነገር በቂ እውቀት ያስፈልገናል ። ሃይማኖትን መለዋወጥም በምድር ላይ ካሉ ጸያፍ ተግባራት አንዱ ነው ። ለገዛ ሃይማኖቱ ያልታመነ ሰውም ለማንም አይታመንም ። ሕሊናን የቅን ፍርድ ማስተማር ይገባል ። የበደለው አባታችን ወይም ልጃችን ቢሆን በቅን መፍረድ ይገባል ። የእኛ ጎሣ የሆነ ሰው በሥልጣን ሲባልግ ማስተባበል ፍርድ የለሽ ቀንን በራስ ላይ መጥራት ነው ። መንግሥታት በተለዋወጡ ቍጥር ተለዋዋጭና የገዳይ አወዳሽ መሆን የቁም ሞት ነው ። ቀጥተኛ ሰው በአእምሮው እንጂ በገንዘቡ ፣ በጎሣው ፣ በስሜቱ አይመራም ። የሰውን ፊት እያየ እውነት ለመናገር መሪውን አያሽከረክርም ። ድሀን እስከ ጥግ እየገሠጸ ባለጠጋን አያፍርም ። ቀጥተኛ ሰው አጋላጭ ሳይሆን ገላጭ ነው ።

ቀጥተኛ ሰው ልቡ ከአፉ ፣ አፉ ከተግባሩ ጋር የተባበረለት ነው ። ቀጥተኛ ሰው በመረጠው መንገድ ከብዙ ሰዎች ጋር ቢጣላም ከሕሊናውና ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም አለው ። እንደሚወድ ለመምሰል አይሞክርም ። ፍቅሩንም ጠቡንም በግልጽ ይናገራል ። ይህ ጠባይ እግዚአብሔርና እግዚአብሔርን የሚወዱ የሚያከብሩለት ነው ። ቀጥተኛነት የእግዚአብሔርን ወዳጅነት ፣ የጻድቃንን ቤተሰብነት የሚያስገኝ ነው ። ፍሬ የሌለውን ገለባ ከመሸከም ፣ ሁለት ፍሬ መልቀም ይሻላል ። የሰው ልጅ ለእውነት የሚያባክነው ጊዜ ትንሽ ነው ፣ ውሸት ለመናገር ግን ዓለምን ይዞራል ። ውሸት ዓለምን በመዞር የታወቀች ብትሆንም ዕድሜዋ አጭር ነው ። ቀጥተኞች የተግባር ሰዎች ናቸው ። የተግባር ሰው የታፈረና የተከበረ ነው ። መንግሥታት እንኳ የሚፈሩት የሚለፈልፈውን ሰው ሳይሆን የተግባር ሰውን ነው ። የተግባር ሰው ልኩ የአንድ ሰው አይደለም ፣ የሺህ ዋጋ ነው ። ሰዎች ሊከተሉን የሚችሉት በተግባር ማሳየት ስንችል ብቻ ነው ። ቀጥተኛነት እውነትን በፍቅር መግለጥ ነው ። ድጦ ማለፍ ሳይሆን መራራት ነው ።

ተቀይሜሃለሁ ማለት የአክባሪነት ውጤት ነው ። ጅልና ሞኝን ደግሞም ወፈፌን የሚቀየመው የለም ። ይህን ካንተ አልጠብቅም ብሎ ከእኛ መልካም ነገር የሚፈልግ ሰው ድምፅ ነው ። የተቀየመን ሰው የሚያከብረን ነውና ልንፈልገው ይገባል ። የጋራ ፍቅር እንዲቀጥል የሚፈልግ ነውና የተቀየመንን መፈለግ አለብን ። በዚህ ዘመን ግን የሚወድም የሚቀየምም የለም ። ዘመናዊነት መረሳሳት ፣ በላ በላ አድርጎ መለያየት ነው ።

ይቀጥላል
ጥቅምት 3 ቀን 2019 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ