የትምህርቱ ርዕስ | ታራቂ

ሕፃናት የይቅርታ ልብ አላቸው ። ተጣልተው ወዲያው ይታረቃሉ ፣ እንባቸው ሳይደርቅ የጎዳቸው ሰው “ጓደኛ እንሁን” ሲላቸው እሺ ይላሉ ። ቤተሰብ ለቤተሰብ እየተጣላ ምክንያት የሆኑት ሕፃናት ወደ ጨዋታቸው ይመለሳሉ ። “የልጅ እናት አባይ ናት” ይባላል ። አባይ/ሲነበብ ላላ ተደርጎ ይነበብ/ ውሸታም ማለት ነው። ልጁ ድንገት ድርቅርቅ ሲልባት ኡኡ ብላ ትጮኻለች ። ጎረቤት ሮጦ ሲገባ ልጁ እየተጫወተ ነው ። በዚህ ምክንያት “የልጅ እናት አባይ ናት” ይባላል ። ልጆች ስሜታዊ ሕመማቸውንም ፈጥነው ይረሳሉ ። ትንሽዋን ጣታቸውን በማውጣት ከተኳረፉት ጓደኛቸው ጋር ይታረቃሉ ፣ እንደ ቀድሞው ይሆናሉ ። በልጆች ጠብ ቤተሰብ ቢጣላ መልሶ ያፍራል ። አዋቂው በቶሎ ይቅርታ ማድረግ አይችልም ። ከስሜታዊ ስብራቱ ለመውጣት ዓመታት ይፈጁበታል ። ስለ እኔ ሁናችሁ ካልተጣላችሁ በማለት የጠብ ደቦ ይሰበስባል ። የብዙ ሰዎች የውስጥ ሰላም መደፍረስ ፣ በሥጋዊና መንፈሳዊ ሕመም ውስጥ ማለፍ አንዱ ምክንያት የይቅርታ ልብ ማጣት ነው ። ሰውዬው አንድ ጊዜ በድሎናል ፣ እኛ ግን ዕለት ዕለት ራሳችንን እንበድለዋለን ። በደሉ ሕያው እንዲሆን የምናደርገው ጥረት እኛን እየገደለን ይመጣል ። ለደረሰብን ችግር ወለድ የምንከፍለው ይቅር ብሎ ባለ መተው ነው ። የዚህ ዓለም ቀኖች ላይመለሱ ይሄዳሉ ፣ ዘመኑም አጭር ነው ። ደስታችንን የሚዋጋውን ቂመኛነትን ከእኛ ማስወገድ ይገባል ።

ፈጽሞ ይቅር ማለት የማይፈልጉ በቀል አርግዘው የሚኖሩ ሰዎች አሉ ። እነዚህ ሰዎች ዓይን ስለ ዓይን በሚለው በብሉይ ሕግ የሚመሩ ሳይሆን ዓይን በሕይወት መከፈል አለበት የሚሉ ናቸው ። ዓይን ስለ ዓይን ፣ ጥርስ ስለ ጥርስ የሚለው የኦሪት ሕግ ከዚያ ያለፈ በቀል ስለ ነበር የተካከለ ፍርድ ለመስጠት ፣ ስህተትን በልኩ ለማየት የተላለፈ አዋጅ ነው ። በቀል በቀልን ይወልዳል ። በቀል ሰላምን አይሰጥም ፣ ጠብን ወደ ትውልድ ያወርዳል ። በቀል የማይመለከተውን ሰውን ማጥቃትም ይሆናል ። አባት በበደለ ልጅ ቢሞት ፍትሕ አይደለም ። በዓለም ላይ ሰላምን የሚያመጣ ፍትሕ እንጂ በቀል አይደለም ። በቀል ሥልጣን ከሌለው ሰው የሚወሰድ የሽንፈት እርምጃ ነው ። ፍትሕ ግን የእግዚአብሔር ዙፋን መገለጫ ነው ። ከሁሉ በላይ በቀልን ለእግዚአብሔር መተው ይገባል ። የእርሱ ፍርድ ይግባኝ የሌለው ፣ በጉቦ የማይወጡበት ፣ አድልኦን ያሸነፈ ነው ። አንዳንድ ሰዎች በደለኝ የሚሉት ሰው ሳይኖር ስለ እርሱ ብዙ ይናገራሉ ፣ ሰውዬው ሲመጣ ደግሞ በፍቅር ያወራሉ ። በድብቅ ስለ ሰውዬው ግፍ እየተናገሩ ፣ በአደባባይ ደግሞ “ለእኔ ልዩ ነው” በማለት ይመሰክራሉ ። እንዲህ ዓይነት አስካሪ ጠባይ ያላቸው ሰዎች አሉ ። እነዚህን ይቅር ማባባል በጣም ከባድ ነው ። ግልጽ መወቃቀስ በሌለበት ግልጽ ይቅርታ ሊኖር አይችልምና ።

የይቅርታ ልብ ያላቸው ሰዎች ሥጋዊ ጤናቸውም ጥሩ ነው ። ቍስላቸው ቶሎ ይሽራል ። የትም ቦታ ላይ መተኛት ይችላሉ ። አንድን ነገር አያልመዘምዙም ። የኋላውን እየተዉ ወደፊት ይዘረጋሉ ። ያ ጊዜ ሊመለስና ሊክሱት አይቻልም ። ይቅርታ ማለት ጉዳት አልነበረም ማለት ሳይሆን ራስን እየመረዙ ላለ መኖር የሚከፈል ዋጋ ነው ። ይቅርታ ሰማያዊ ጠባይ ነው ። ሰው መበደል ይችላል ፣ ይቅር ማለት ግን ይከብደዋል ። ይቅር ሲል መለኮታዊ ጠባይን እየተለማመደ ነው ። ሰዎችን በበቀል ከምናስተምራቸው ይልቅ በይቅርታ ራሳቸውን እንዲያዩ እናደርጋቸዋለን ።
ሰው ሲበቀል ከጠላቱ ጋር እኩያ ይሆናል ፣ ይቅር ሲል ግን ጠላቱን ይበልጣል ይባላል ። ይቅርታ ብልጫነት ነው ። ይቅርታ ሰውነትን መቀበል ነው ። ይቅርታ ለነገ ስህተታችን የምናስቀምጠው ንጹሕ ውኃ ነው ። ይቅር የምንለው ይቅር የሚባል ደካማነት ስላለን ነው ። ይቅር ስንል ሰውዬውን እንደ ራሳችን ወደድነው ማለት ነው ። ከራሳችን ጋር የምንኖረውም በይቅርታ ነውና ። ብርጭቆ የሰበረውን ሰው ከመጠን በላይ ስንቆጣው ልቡን እንሰብረዋለን ። ቍጣዎቻችን ተመጣጣኝ አይደሉምና ልናስወግዳቸው ይገባል ። ደግሞም እኛን ለማገዝ ወይም እኛን ለማስደሰት ብለው አሳዝነውን ከሆነ መመርመር አለብን ። ቂም በአካል የራቅነውን ሰው በልባችን ላይ የማይከፍልበት ውድ ክፍል ሰጥተን ማስቀመጥ ነው ። ይቅር ማለት ትውስታን መሰረዝ ሳይሆን ያለ ምሬት ማስታወስ ነው ። አይረሳም ግን አይነሣም እንዲሉ ።

ያዘንበት ሰው የታሰረ ሰው ነው ። መታሰሩን ሳያውቅ ለመሮጥ ይነሣል ፣ ግን ይወድቃል ። ይቅርታ ሁለታችንንም መፍታት ነው ። እውነተኛ ነጻነት የሚገኘው በይቅርታ ነው ። ደግሞም ሰዎች ካሳጡን ነገር እግዚአብሔር የሰጠን ይበልጣል ። የሚደንቀው ይህ ሁሉ ጠላት መመረቱ ሳይሆን በዚህ ሁሉ ጠላት መካከል በሕይወት መኖራችን ነው ። ሕፃን ከጉዳቱ በፊት የነበረውን ጨዋታ ያስባል ፣ እኛ ግን ከጉዳቱ በፊት የነበረውን መልካምነት ማሰብ ይሳነናል ። አድገናል ብለናል ፣ ማደግ መልካሙን መጣል ነው ወይ ? ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን ።

ይቀጥላል

ጥቅምት 9 ቀን 2019 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ