የትምህርቱ ርዕስ | የምድር ጨው ናችሁ -2

“እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤” (ማቴ. 5 ፡ 13 ) ።

እንባ ጨዋማ ነው ። እንባ ዓይን እንዳይደርቅ ፣ የተለያዩ ብናኞችን ለማጠብና ጥቃቅን ነፍሳትን ለመከላከል ይረዳል ። እንባ ጨዋማ በመሆኑ ዓይን የማጠብ ሥራ ይሠራል ። እንባ ስሜታዊ መልእክተኛም ነው ። በጣም ደስ ሲለንና ነገሮች ከጠበቅነው በላይ ሲሳኩልን የሚቀናን እንባ ነው ። እኔ ማን ነኝ ? በማለት የዕድለኝነት ስሜታችንን የምንገልጠው በእንባ ቋንቋ ነው ። ሲከፋንና ስናዝን እንባችን ይፈሳል ፣ ውስጣችንም ፋታ ያገኛል ። ስሜቱ የነፍስ ሲሆን እንባው የሥጋ ነው ። ሁለቱም ተዋሕደዋልና ኀዘናቸውንና ደስታቸውን ይገልጣሉ ። እንባ በጣም ጥቂት ፈሳሽ ቢሆንም ከውቅያኖስ በላይ ለማየት ይከብዳል ። እግዚአብሔርም እንባን አያልፍም ። እንባ ያለበት ሰውም አይቀናውም ። እንባ ጥሩ ትራስ ለገዛ ግፈኛ የእሾህ ጉዝጓዙ ነው ። እንባ ማታን ድርብ ጨለማ ያደርጋል ።

ክርስቲያን የምድር ጨው ነው ። ሰዎች አጥርተው እንዲያዩ ያግዛል ። የእውቀትን ብርሃን ይገልጣል ። ዕይታን የሚጎዱ ነገሮችን ፣ ማስተዋልን የሚያሳጡ መንፈሳዊ ችግሮችን ይዋጋል ። ውሸትን ብቻ ሳይሆን የተበረዙ እውነቶችንም አጥርቶ ያሳያል ። በዚህም ከዋሾዎች ጠላትነትን ያተርፋል ። ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይለዋል ፣ ካዘኑት ጋርም ያዝናል ። በማንም በጎ ዕድል አይበሳጭም ፣ በማንም ውድቀትም አይደሰትም ። ክርስቲያንነት ማኅበራዊ ኑሮን የሚሸሽ ሳይሆን የሚያከብር ነው ። እውነትን ይገልጣል እንጂ ውሸታም ነህ እያለ አይሳደብም ። መንገዱን ያሳያል እንጂ እገሌ አይድንም እያለ ፍርድን አይሰጥም ።

ላብ የጨው ጣዕም አለው ። ላብ የድካም ፣ የጥረት ውጤት ነው ። ላብ መንገደኛው ሲደክመው የሚታይበት ርጥበት ነው ። ላቡን ቢተወዉ የጨው መልክ በገላው ላይ መታየት ይጀምራል ። ላብ በዋናነት የሠራተኞች መገለጫ ነው ። የላብ እንጀራ ከሰማይ የተፈቀደች ናት ። መጽሐፍ መብል እየወደዱ ሥራ የሚጠሉትን ይነቅፋል (2ተሰ. 3፡10)። የላብ እንጀራ ጣፋጭ ናት ። የላብ እንጀራ አስደሳች እንቅልፍ አላት ። ደመወዙ ምንም ይሁን ሰው ወጥቶ የሚገባበት ሥራ ካለው ፣ ላቡን አፍስሶ ከተመገበ ደስታ አይርቀውም ። ልፋተኞች አእምሮአቸው ሰላም ነው ። የሚፈልጉት የዕለት ጉርስ ነውና በትንሹ የመደሰት ጸጋን አግኝተዋል ። ክርስቲያን የምድር ጨው ነው ። ያለፋበትን አይበላም ። የግፍ እንጀራን ይጸየፋል ። ጉቦ ልጆችን እንደሚያሳብድ ተረድቶ የሙስና ገንዘብን ይሸሻል ። ለትውልዱም ረመጥን አያስቀምጥም ። ክርስቲያን የሌሎችን ልፋት ያከብራል ። ለሠራተኛው ደመወዙ እንደሚገባው ያምናል ።

እየሮጡ ያሉ የወንጌል አገልጋዮችን ፣ የለፉ ሰባክያንን ያግዛል ። የአፋቸው ዘበኛ ሆኖ ለምን በሉ ፣ ምን በሉ እያለ አይተችም ። በነፍስ ያገለገሉንን በሥጋ ፍላጎታቸው ማገልገል ፣ መብልና ልብስን መስጠት ይገባል ። መንፈሳዊ ሰው የእግዚአብሔር አገልጋዮችን የሚያከብረው እጅ በመንሣት ፣ አንቱ ብሎ በመጥራት ሳይሆን በሚያስፈልጋቸው በመድረስም ነው ። የሰው እውነተኛ ክብሩ ረሀቡ መወገዱ ነው ! ሁሉም ሰው ጌታን እቤቱ በእንግድነት ቢቀበል ደስ ይለዋል ። በነ ማርታና በነ አልዓዛርም ይቀናል ። አገልጋዮችን መቀበል ክርስቶስን ራሱን መቀበል እንደሆነ ቃል ኪዳን ያለው ትእዛዝ አለ (ማቴ. 10፡41-42) ። ሐዋርያው ጳውሎም እንዲህ ይላል፡- “በመልካም የሚያስተዳድሩ ሽማግሌዎች ፥ ይልቁንም በመስበክና በማስተማር የሚደክሙት ፥ እጥፍ ክብር ይገባቸዋል ። መጽሐፍ፡- የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር ፥ ደግሞ፡- ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል ይላልና ።” (1ጢሞ. 5 ፡17-18) ።

ይቀጥላል
ጥቅምት 25 ቀን 2019 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ