የሰው ልጅ የተገለጠና የተሰወረ ሕይወት አለው ። ቤታችን ጓዳና ሳሎን ሲኖረው ሳሎን የምናስገባውና ጓዳ የምናስገባው ሰው አለ ። ሁሉንም ጓዳ ማስገባት ራሱን የቻለ ጉዳት ያመጣል ። ሰዎች የሚወዱንና የሚያከብሩን ስለ እኛ የማያውቁት ነገር ካለ ብቻ ነው ። ሁሉንም ካሳየናቸው በሙሉነት ያወቁን ስለሚመስላቸው ንቀትን ይጀምራሉ ። እኛ ብቻ የምናውቀው ፣ እግዚአብሔር ብቻ የሚያውቀው ፣ መንፈሳዊ አባቶች ብቻ የሚያውቁት ፣ ሐኪም ብቻ የሚያውቀው ፣ ትዳራችን ብቻ የሚያውቀው ፣ ወዳጃችን ብቻ የሚያውቀው ምሥጢር ሊኖረን ይገባል ። በምድር ላይ ገመና የሚባል ነገር ባይኖር ልብስ መልበስ ፣ ቤት ማደር ፣ ንስሐ አባት መያዝ ፣ አማካሪ ዘንድ መሄድ ባላስፈለገ ነበር ። ሕይወት ጣዕም የሚኖራት ምሥጢር ሲኖር ነው ። ሁሉም ነገር አይወራም ፣ ሁሉም ነገር አይደበቅም ። ሚዛናዊነት የሰው መገለጫ ነው ። ውሎአችን በሙሉ ከታወቀ ፣ ኑሮአችን በሙሉ አደባባይ ከወጣ ይህ ከፍተኛ የሆነ የአእምሮ መቃወስ ነው ።
ስንበላ ስንጠጣ ፎቶ እየተነሣን መልቀቅ ተገቢ አይደለም ። የራበውን እናሳቅቀዋለን ፣ እነ እገሌ እንዲህ በገንዘብ ሲጨማለቁ ምነው እኔን ረሳኸኝ ? ብሎ አምላኩን እንዲያማርር እናደርገዋለን ። የማናካፍለውን ምግብና ደስታ እወቁልኝ ማለት ተገቢ አይደለም ። የብዙዎቻችን ኑሮ ሌሎችን ለማናደድ ከፍተኛ ወጪ የምናወጣበት ነው ። መኖር ያለብን ፣ መዝናናትም የሚያስፈልገን ጠላታችንን ለማናደድ ሳይሆን ለእኛ አስፈላጊ ከሆነ ብቻ ነው ። ለብሽሽቅ መኖር ተገቢ አይደለም ። ውድ ልብስ ለብሰው የሚታዩ ፣ ቅንጡ ሕይወት ላይ ነኝ ለማለት ያማረ ፎቶ የሚለቁ ሰዎች አብዛኛዎቹ ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ የሚያልፉ ናቸው ። ያንን ጭንቀት ሰው ያየባቸው ስለሚመስላቸው በልብስና በጌጥ ለመሸፈን ይሞክራሉ ። ለጭንቀት የሚያስፈልገው መንፈሳዊ እርዳታ ፣ የሙያ እገዛ እንጂ ጌጥ አይደለም ። በሸፈነው ቍጥር ይበልጥ እየጎዳን ይመጣል ። በጣም ደስተኛ እየመሰሉ የሚታዩ ሰዎች በቀጥታ ስርጭት ራሳቸው ላይ ጉዳት ሲያደርሱ እናያለን ። የተውኔት ኑሮ ስለሚያደክም እነዚህ ሰዎች ደክሞአቸዋል ። ታይታ መውደድ ግላዊ ሕይወትን እንድንሰርዝ ያደርገናል ። አንድ ሰው ጤነኛ ነው የሚባለው ልብሱን አውልቆ ዕርቃኑን ባለ መቆሙ ፣ ሁሉንም ነገር ባለ መናገሩ ነው ። በአደባባይ ወጥተው እንደ በረታ ሰው ለመታየት የሚሞክሩና በርቱ የሚሉ ሰዎች ብዙ ጊዜ በተሰወረ ስቃይ ውስጥ የሚያልፉ ናቸው ።
መንግሥታት ሊገቡበት የማይገባ የዜጎች ግላዊ ድንበር አለ ። ያንን አልፈው በሰው ግላዊ ኑሮ ማዘዝ ከጀመሩ አደገኛ ቀጠና ውስጥ ገብተዋል ማለት ነው ። መንግሥታት የሚመለከተንና የማይመለከተን ነገር አለ ብለው ማመን አለባቸው ። ልክ እንደዚሁ የእኛ ሕይወት የሚመለከታቸውና የማይመለከታቸው ሰዎች አሉ ። በሰዎች ሕይወትም ድንበራችንን ጠብቀን መቅረብ ያስፈልገናል ። አሊያ ሰዎች እየራቁንና በሩን እየዘጉብን ይመጣሉ ። አማካሪዎች ስንሆን ብዙ ነገሮችን ልንጠይቅ እንችላለን ። የማንረዳውን ሰው መቆስቆስ ግን የረሳውን ሕመሙን ማባባስ ነው ። አንድ ማኅበረሰብ ፈርሷል የሚባለው ግላዊ ችግሮች የአደባባይ የጨዋታ ርእስ ሲሆኑ ነው ። አንተ እያለቀስህ ያወራኸው የትዳርህ ምሥጢር ለሥራ ፈቶች የወሬ ርእስና ቀኑን መርሻ ነው ። የት ቦታ ልብስህን ማውለቅ እንዳለብህ ካላወቅህ የነገ ነጻነትህን አሳልፈህ ትሰጣለህ ። የደረሰብህን ብትረሳው እንኳ የሰሙት አይረሱትም ። ሰው አደባባይ ከወጣ ትዳሩ ፣ ጓደኝነቱ ፣ የሃይማኖት አባቱ ፣ አቅሙ ከድቶታል ማለት ነው ።
አንድ የታመሙ መነኮስን እያስታመመ ያለ ጎልማሳ ፊታቸውን ሲያጥባቸው በቪድዮ ቀርፆ ሲለቅ አይቻለሁ ። ለታመመ የፊት ውኃ ማቅረብ ብርቅ እየሆነ መምጣቱን አመላካች ነው ። የትዳር አጋራቸውን ጥሩ እራት አቅርበው የሚጠብቁ የቀጥታ ስርጭት ላይ ሁነው ነው ። እራት አቀረብኩኝ እልል በሉልኝ እያሉ ነው ። አንድ ዲያቆን ወደ ሩቅ ገዳም ለሱባዔ ሄዶ የየቀኑን ውሎ በቀጥታ ስርጭት ሲያስተላልፍ እያየን ነበር ። የሚያሳዝነው ዓለምን ንቀው የሄዱ የመነኮሳትን ኑሮ ሳይቀር ያለ ፍላጎታቸው አደባባይ ማውጣቱ ነው ። ጸሎት አደባባይ/ታይታ ከሆነ ምሕረት ማግኘት ከባድ ነው ። አባት እናትን ስንሸልም እንዴት ለአደባባይ ግባት እናውለዋለን ? ሰውረው ያሳደጉንን አደባባይ ማውጣት ተገቢ አይደለም ። የተወራለት ሰው ዕድሜው አጭር ነው ። የታየ ሰው ብዙ አይበረክትም ። አቤት አቤት የተባለለት ሰው ለመጠውለግ ይቸኩላል ። መሪዎች እንኳ ዕድሜአቸው የሚረዝመው ስለሚረገሙ ነው ። በእግዚአብሔር ፍትሕ ስለምንገባ እኛ ፈርደን እስክንጨርስ እግዚአብሔር ዝም ይላቸዋል ። በዓለም ላይ ብዙ የተወራለት ነገር አይበረክትም ። ፍቅራችሁንም በጣም አታውሩ ። አልማዝና ወርቃችሁን ፊት ለፊት አታስቀምጡትም ። የምትወዱትንም ሰው ደብቁት ። የቀደሙት ልጆቻቸውን ሊያሳዩ አይደለም ትኩር ብለው ራሳቸው አያዩአቸውም ነበር ። አይቼው ጣዖት ቢሆንብኝና ቢሰበርስ እያሉ ይጠነቀቁ ነበር ። ኑሮን ከኖሩት መማር መልካም ነው ።
ያደረግነውን መልካም ነገር አደባባይ ማውጣት ፣ ለእናታችን የሰጠነውን ፍቅር እዩልኝ ማለት ይህን ማድረግ አይገባኝም ነበር እንደ ማለት ነው ። መጽሐፉ፡- “እንዲሁ እናንተ ደግሞ የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ፡- የማንጠቅም ባሪያዎች ነን ፥ ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል በሉ” ይለናል (ሉቃ. 17፡10) ። ሦስት ነገሮችን እናስተውል የታዘዝነውን እናድርግ ። ሁለተኛ እግዚአብሔር በእኔ ሠራ እንጂ በእኔ ጉልበት ይህ አልሆነም ብለን እናስብ ። እግዚአብሔር በእኔ ድንቅ አደረገ ብሎ አደባባይ ማውራትም የታይታ ጥማት ሊሆን ይችላል ። ክብሩን እግዚአብሔር ይውሰድና እያሉ ክብርን ለራሳቸው የሚሰበስቡ አሉ ። የታዘዝነውን ማድረግ ፣ እንዳደረግን ለራሳችን እንኳ አለመንገር ይገባል ፤ ሦስተኛ ላደርገው የሚገባኝን ነው ያደረግሁት ብሎ ለሚመጡ ሙገሳዎች ቁርጠኛ መልስ መስጠት ይገባል ። “ድምፅህ በጣም ያምራል” ቢሉት የቂርቆስ ዲያቆን፡- “ያውም ጉንፋን ይዞኝ ነው” ብሏል ።
ይቀጥላል
ኅዳር 3 ቀን 2019 ዓ.ም.